የዓለም የኤች አይቪ ኤድስ ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ፡፡

“ ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው” (Community Make the Difference ) በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በአቢሲኒያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የየተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤች አይቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር “ ማህበረሰብ የለውጥ አቅም ነው” (Community Make the Difference ) በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በአቢሲኒያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የየተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣መምህራንና ተማሪዎች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በፕሮግራሙ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ክቡር አቶ ዳኛው ገብሩ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት የተሻለ ግንዛቤ ተፈጥሮ የበሽታውን ስርጭት መቆጣጠር የተቻለበት ደረጃ ደርሰን የነበረ ቢሆንም አሁን በተፈጠረው መዘናጋት በሽታው እንደገና ስርጭቱ እየጨመረ የመጣበት ሁኔታ እንዳለ አስታውሰው በተለይም ይህ በሽታ የሚያጠቃው ወጣቱን በመሆኑ ግንዛቤውን ለመፍጠርና መነቃቃትን ለመፍጠር በትምህርት ቤት ደረጃ በዓሉን ማክበር አስፈልጓል ያሉ ሲሆን በተለይም በሽታውን ለመቆጣጠር ሁላችንም ርብርብ እናድርግ እራሳችንንም እንጠብቅ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢፌዲሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ክብርት ወ/ሮ ፂዮን ተክሉ በበኩላቸው ይህ አስከፊ በሽታ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በማስታወስ በተለይም ከቅር ጊዜ ወዲህ በሽታው ጠፍቷል በሚል መዘናጋት እንደገና የሀገራችን ዜጎች እያጠቃ መምጣቱን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ወጣቱ ላይ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው አብዛኛው ወጣት በትምህርት ቤት እንደመገኘቱ ግንዛቤውን በመጨመር እራሱን እንዲጠብቅ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር ደኤታዋ አክለውም ለበሽታው አጋላጭ የሆኑ ባህሪያትን በመለየት እርምጃ በመውሰድ እና ተግዳሮቶችን በመፍታት ከፍተኛ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የሁሉንም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎችን ግንዛቤ በማሳደግና በተለይ ተማሪወች ራሳችሁን በመጠበቅ የነገ ሀገር ተረካቢ እንድትሆኑ የበኩላችሁን ልትወጡ ይገባል ማለታቸውን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዘግቧል፡፡