የኮቪድ-19 ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ፡፡

ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፉት ወራት ኮቪድ-19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተከናወኑ ዋና ዋና ስራዎችንና በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የጤና ሚኒስትር  ክብርት ዶ/ር ሊያ ታደሰ በመግለጫው ወቅት እንደገለፁት የኮቪድ-19 ስርጭት ከሌሎች ሀገራት አንፃር ቁጥሩ አነስተኛ ቢሆንም ቀላል የሚባል ግን አይደለም፤ ነገር ግን ኮቪድ-19 ከሚያስከትለው የጤና ችግር ባሻገር በኢኮኖሚና በስነልቦና ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ ከጥንቃቄ ጋር እንቅስቃሴዎችን መፍቀድና ትምህርት ቤቶችን መክፈት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡ በመቀጠልም እንቅስቃሴዎች እየተካሄዱ የመከላከል ስራዎችን ለመተግበር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም በትምህርት ቤት የመከላከል ስራውን ለማጠናከር ከትምህርት ቤት አስተዳደሮች በተጨማሪ ወላጆች ድርሻ ያላቸው በመሆኑ በመመሪያው እንደተገለፀው ልጆች ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት የህመም ስሜት መኖር አለመኖሩን ወላጆች ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የህመም ስሜት ካላቸውም መሄድ የለባቸውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ኤባ አባተ በበኩላቸው ኮቪድ-19  ሁለት ምዕራፎች አሉት አንዱ ስለወረርሽኙ ምንም ያላወቅንበት ጊዜ ሲሆን ሁለተኛው ስለመከላከያው ያወቅንበት ጊዜ ነው፤ቀድሞ ዝግጅት በማድረግና በቅንጅት በመስራታችን በምዕራፍ አንድ የኮቪድን19 ተፅዕኖዎች መቀነስ ችለናል፡፡ ምዕራፍ ሁለትን ደግሞ ኮቪድ-19 እየተከላከልን ስራ መስራት እንችላለን በሚል ሀሳብ የመከላከያ መመሪያዎችን እየተጠቀምን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የአስከሬን ምርመራ እናደርግ የነበረው ከሟች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለመለየትና ስርጭቱን ለመግታት ነበር አሁን ግን የማህበረሰብ ስርጭቱ ከፍተኛ ስለሆነ ቆሟል ብለዋል፡፡
በመድረኩ አጠቃላይ ወረርሽኙ ያለበትን ሁኔታ በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር  አቶ አስቻለው አባይነህ ወረርሽኙ ወደፊት ለሚከሰት ችግር ትምህርት የተቀሰመበት መሆኑን ጠቅሰው ቀድሞ መዘጋጀት፣ ባለሙያዎችንና ማህበራትን ማቀናጀት፣ ያለውን ሀብት መለየትና መጠቀም፣ በወቅቱ መረጃ መለዋወጥ፣ አስገዳጅ ለይቶ ማቆያን መተግበር፣ ከፍተኛ ባለስልጣናትን ለንቅናቄ መጠቀም እንዲሁም ሌሎች የጤና አገልግሎቶች እንዳይቀዛቀዙ መስራት መልካም ተሞክሮዎች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በመረጃቸው እስከ ቅርብ ጊዜ ምልክት የማያሳዩ ሰዎች ከ90 ፐርሰንት በላይ የነበሩ ሲሆን ከባለፉት 2 ሳምንታት ወዲህ ግን ወደ 63.1 ዝቅ ማለቱንና ወደ ፅኑ ኅሙማን ህክምና የሚገቡት ቁጥር መጨመሩን ገልፀዋል፡፡ ከእድሜ አንፃርም 57 ፐርሰንት ያህሉ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ዕድሜ  ከ15-34  ሲሆን 51.9 የሞት መጠን የተመዘገበው ግን  ዕድሜያቸው ከ60 በላይ በሆኑ ሰዎች በመሆኑ ሁላችንም ለሌሎች ሞትና ህመም ምክንያት ባለመሆን ራሳችንንና ሎሎችን እንታደግ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡