ስንፈተ ወሲብ ወጣት ወንዶች ላይ

የብልት አለመቆም ከ10 እስከ 20 ከመቶ ወንዶች ላይ የሚያጋጥም ክስተት ነው። ድንገት ሲከሰት ድንጋጤና ሀፍረት ይፈጥራል።

በቀጣይ ፆታዊ ግንኙነት ላይም "ዛሬም አልቆም ቢለኝስ?" የሚል ፍርሀት ይኖራል።

የብልት አለመቆም መንስኤዎች አካላዊ ወይም ስነልቦናዊ ሊሆኑ ይችላሉ። መቆም ማለት ብልት በደም ሲሞላ የሚከሰት ስለሆነ የደምስር ላይ ተፅእኖ የሚያደርጉ ህመሞች አሉታዊ ተፅእኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። ለምሳሌ፦ የስኳር ህመም፣ የደም ግፊት፣ ከፍተኛ ኮሌስትሮል። በተጨማሪም ፕሮስቴት እጢ፣ የነርቭ ህመሞች....ወዘተ ስንፈተ ወሲብ ሊያመጡ ይችላሉ።

ከ40 አመት በታች የሆነ ሰው ላይ ሲከሰት ግን አብዛኛው መንስኤው ስነልቦናዊ ነው። በእግሊዘኛ ባለሁለት ስንኝ ግጥም አለች።
        If your mind is ifffy
        You can't get a stiffy

ውርስ ትርጉም   "ጭንቅላትህ የሆነ ነገር ከተጠራጠረ፣
                           ታች ያለው ነገር ደም ሞልቶ አይወጠረ።

3 ስነ ልቦናዊ የስንፈተ ወሲብ ምክኒያቶች አሉ። ጭንቀት(ፍርሀት)፣ ንዴት እና ፀፀት ናቸው። እነዚህ ስሜቶች አንዳንድ ጊዜ ግልፅ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ግን ከአስተዳደግ ጀምሮ የመጡ ተፅእኖዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ሁሉም የስነ ልቦና ህክምና በማድረግ ይስተካከላሉ።

በማህበራዊ ሚዲያ "ለስንፈተ ወሲብ የሚጠቅሙ ምርቶች" በብዛት ይተዋወቃሉ። ነገር ግን ሙሉለሙሉ ስነልቦናዊ ለሆነ ችግር መድሀኒት መውሰድ አየር ማረፊያ ሄዶ መርከብ እንደመጠበቅ ነው። ብዙ ሰዎች ብዙ ብር አውጥተው  የሚጠብቁትን ውጤት አላገኙም።

ያለ አእምሮ ጤና፤ ጤና የለም።
ዶክተር ዮናስ ላቀው