የኮሮና ቫይረስ እና ሕፃናት

በአለማችን ፈታኝ የሆነው የኮሮና ቫይረስ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወዲህ በኮሮና ቫይረስ  የሚያዙና ህይወታቸውን የሚያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት 64‚301 ያህል ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሲሆን ከእነዚህም ወስጥ 644 የሚሆኑት ከ 0 እስከ 4 አመት ያሉ ሕፃናት ሲሆኑ 788 ያህሉ ደግሞ ከ 5 እስከ 14 አመት ያሉ ሕፃናት ልጆች ናቸው፡፡ህፃናት ልጆችም በኮሮና ቫይረስ ተይዘው እንደ አዋቂውች ምንም የህመም ስሜቶች ወይም ቀላል የህመም ስሜቶች ሊያጋጥማቸው ሲችል ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የመግባታቸው እድል ግን ዝቅ ያለ ነው፡፡
አቶ ሄኖክ ሀይሉ በብሔራዊ የሕብረተሰብ ጤና አደጋ ማስተባበሪያ ማዕከል የኮቪድ-19 የህክምና አገልግሎት ተቋማት ዝግጅት እና የቤት ውስጥ ራስን ለይቶ ህክምና (ውሸባ) እንክብካቤ ክፍል ሀላፊ እንደተናገሩት፤የኮሮና ቫይረስ ከጨቅላ ህፃናት ጀምሮ የሚይዝ በሽታ ሲሆን ህፃናቱ ምንም አይነት የህመም ምልክት ላያሳዩ  ወይም ቀለል ያለ የህመም ምልክቶች ሊኖራቸው ቢችልም ወደ ሌላው የማህበረሰብ ክፍል ግን ቫይረሱን ያስተላልፋሉ፡፡ ህፃናት ልጆች በሽታን የመከላከል አቅማቸውን ለማጎልበት ቤተሰቦች አቅማቸው በሚችለው መጠን ለልጆቻቸው  የተመጣጠነ ምግብ ቢመግቡ ተመራጭ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ተጎዳኝ ህመም ላለባቸው ልጆች ልዩ እንክብካቤ ማድረግ ይገባቸዋል ፡፡ልጆች በአሁኑ ሰዓት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ ወደ ውጪ ወጥተው መጫወት ስለማይችሉ ወደ ትምህርት ቤት ስለማይሄዱ፣ጓደኞቻቸውጋር ስለማይገናኙ ጭንቀት፣ድብርት እና የተለያዩ የባህሪ ለውጥ ሊያሳዩ ይችላል፡፡ ስለሆነም በቤት ውስጥ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ቀለል ያለ ጤንነታቸውን እንዲሁም  በአጠቃላይ የህፃናቱን ሁኔታ ያገናዘበ የቤት ውስጥ ስራዎችን በመስራት፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ፣የተመጣጠኑ ምግቦችን በመመገብ ይሄን ጊዜ ማሳለፍ እንዳለባቸው ገልፅዋል የተለየ የህመም ስሜት እንደ ሳል ትኩሳት፣የአየር/ማጠር፣ቶሎቶሎ የመተንፈስ እና ሌሎች የበሽታ ምልክቶች ካየንባቸው ወደ ጤና ተቋማት መውሰድ እና አስፈላጊውን የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ልብ ይበሉ! የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል በምናደርገው ጥንቃቄ ለልጆቻችን የሚያስፈልጉ የህክምና ክትትሎችን መዘንጋት ተጨማሪ የጤና እክል እንደሚያስከትሉ አንዘንጋ፡፡ስለሆነም ህፃናት በቂ የቀጥታ የፀሀይ ብርሀን እንዲያገኙ ማድረግ ፣ የእናት ጡት ወተት እስከ 2 አመት ድረስ (ከ6 ወር በኃላ ከተጨማሪ ምግብ ጋር) መመገብ እንዲሁም የክትባት ጊዜያቸውን በጠበቀ መልኩ እና በተለያየ ጊዜ ለተላላፊ በሽታዎች ማስከተብ የሚኖርብንን ክትባት እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡   
በዚህ ወቅት ግዴታ ሆኖ ህፃናት ልጆቻችንን ይዘን ከቤት ከወጣን ከሁለት አመት በላይ ለሆኑ ህፃናት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያወልቁ፣የእጃቸውን ንፅህና እየጠበቅን ርቀታቸውን በመጠበቅ ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ባለመሆን ራሳችንን እና ልጆቻችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ።