የኳራንቲን እና የድንበር ላይ ጤና ቁጥጥር

በአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ ወቅት የኳራንቲንና የድንበር ላይ ጤና በመጠበቅ በኩል በርካታ ስራዎች የተሰሩ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ነገር ግን ከአዋጁ መነሳት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ አጠቃላይ የኮሮናን ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ  ጤና ኢንስቲትዩት በተለያዩ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ መመሪያ አውጥቷል፡፡በዚህም መሰረት የኳራንቲን እና የድንበር ላይ ጤና ቁጥጥርን በተመለከተ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ አለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች በኩል የኮሮና ቫይረስ የRT PCR ምርመራ ውጤት ይዞ የሚመጣ መንገደኛን በተመለከተ ከትራንዚት መንገደኛ በስተቀር በአገሪቱ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ በኩል የሚገባ ከአስር አመት ዕድሜ በላይ የሆነ ማንኛውም ተጓዥ ከመጣበት ሀገር ከ 120 ሰዓት ወይም አምስት ቀን በላይ ያልሆነው የተረጋገጠ የRT PCR ምርመራ ኔጌቲቭ ውጤት ይዞ መምጣት እንደሚገባውና እና  መንገደኛው በአየር መንገዱ የጤና ምርመራ ዴስክ የሙቀት እና የኮቪድ-19 ምልክቶች ልየታ ከተደረገ በኋላ አድራሻው ተመዝግቦ ለ7 ቀናት በቤቱ ራሱን ለይቶ የመቆየት ግዴታ እንዳለበት በመመሪያው ተገልጻል፡፡
ነገር ግን በአገሪቱ አለም አቀፍ አየር መንገዶች በኩል የሚገባ ማንኛውም ተጓዥ የኮቪድ-19 ምልክት የሚያሳይ ከሆነ መንግስት በለያቸው ጊዜያዊ ለይቶ ማቆያ እንዲገባ ተደርጎ በተቀመጠው የኮቪድ-19 የህክምና ማንዋል መሰረት ክትትል የሚፈጸም መሆኑን እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ፖዚቲቭ የሆነ ማንኛውም ሰው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የማይችልና የተከለከለ መሆኑን በመመሪያው ተብራርቷል፡፡
በአገሪቱ አለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች የሚገቡ ከስደት ተመላሾችን በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ  ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ከሚመጡበት ሀገር 120 ሰዓት ወይም አምስት ቀን በላይ ያልሆነው የተረጋገጠ የRT PCR ኔጋቲቭ ምርመራ ውጤት ይዘው እንዲመጡ የሚደረግ መሆኑንም በመመሪያው ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ማንኛውም ከስደት ተመላሽ እና ወደ ሀገር የሚመጡ ሰዎች 120 ሰዓት ወይም አምስት ቀን በላይ ያልሆነው የተረጋገጠ የRT PCR ኔጋቲቭ ምርመራ ውጤት ይዘው ካልመጡ፣ ለRT PCR ምርመራ ናሙና ተወስዶላቸው አድራሻቸው ተመዝግቦ ውጤቱ እስኪመጣ ድረስ በቤታቸው እራሳቸውን ለይተው የማቆየት ግዴታ ያለበቸው ሲሆን የምርመራ ውጤቱ ኔጋቲቭ ከሆነ አስፈላጊው ምክር ተሰጥቷቸው እስከ 7ኛው ቀን ድረስ በቤታቸው ራሳቸውን  ለይተው እንዲቆዩ እንደሚደረግ፤ነገር ግን የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤት ፖዚቲቭ ከሆነ በተቀመጠው የኮቪድ-19 የህክምና ማንዋል መሰረት ህክምና እና ክትትል እንዲያገኙ የሚደረግ መሆኑን በወጣው መመሪያ በዝርዝር የቀረበ መሆኑ ታውቋል፡፡