የኩላሊት በሽታ ምንድነው መነሻዎቹስ?

ኩላሊት መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ከሰውነት ለማስወገድ ትርፍ ውሃን ከደም ውስጥ ለመቀነስና የደም ግፊትን ለመቆጣጠር ይረዳሉ፡፡

ሰዎች ሁለት ኩላሊቶች ያሏቸው ሲሆን በግ ራና በቀኝ ከጎድን አጥንት መጨረሻ አከባቢ የሚገኙ ሲሆን በተለያየ መንገድ  ጉዳት በደረሰባቸው ግዜ የኩላሊት በሽታ ይከሰትና የዘወትር ተግባራቸውን ስለሚያውክባቸው የበሽታው መገለጫ የሆኑ ምልክቶችን ያሳያሉ፡፡ ይህም እንደ ጉዳቱ መጠንና ምክንያት ቀላልና በፍጥነት  የሚያገግሙ ወይም የኩላሊቱን ተግባር በፍጥነት የሚያሰናክሉ አልያም በግዜ ሂደት እያዳከሙት ከጥቅም ውጭ ሊያደርጉ( ኪድኒ ፌይለር ሚያመጡ) ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

  የኩላሊት ተግባራት ምንድናቸው?

  • የውሀና ንጥረ ነገሮችን ሚዛና( እንደ ጨው፣ፖታሽየምና ፎስፈረስ ያሉትን) ይጠብቃል
  • ከምግብ መፈጨት፣ከአካል እንቅስቃሴ ወይም ለኬሚካሎች ከተጋለጡ በኋላ ሚኖሩትን ቆሻሻዎች ከደም ውስጥ ያስወግዳል
  • የደም ግፊትን ለመቆጣጠር የሚያገለግለውን ሬኒን የተባለ ንጥረ ነገር ያመርታል
  • ሰውነት የቀይ ደም ሴልን እንዲያመርት የሚያደርገውን ኢሪትሮፓኤቲን የተባለ ኬሚካል ያመርታል
  • ሰውነት ሊጠቀመው የሚችለውን የቫይታሚን ዲ ( vit. D) አይነት ያመርታል

የኩላሊት በሽታዎች  ድንገተኛ እና  ከራሚ በሚል በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡

ድንገተኛ የኩላሊት ጉዳት

ድንገተኛ የኩላሊት ጉዳት ( መድከም) የሚያጋጥመው የሚከተሉት ሁኔታዎች ሲኖሩ ነው፡፡

  • ወደ ኩላሊት የሚደርሰው ደም መጠን ከበቂ በላይ እና ከበቂ በታች ሲሆን
  • ኩላሊት በቀጥታ ጉዳት ሲያገጥመው እና  ሽንት ወደ ኩላሊት  በሚመላለስበት ግዜ ሲሆን እነኝህ የሚከሰቱት ደግሞ በሚከተሉት ሁኔታዎች ነው፡፡
  • ደም መፍሰስ የሚያስከትል አካለዊ ጌዳት ሲገጥም
  • ከፍተኛ የፈሳሽ እጥረት ሲኖር ወይም የበዛ የጡንቻ ስብርባሪ በመኖሩ ምክንያት ከፍተኛ ፕሮቲን ወደ ደም ውስጥ በሚገባ ግዜ
  • በከፍተኛ ኢንፌክሽን ወይም የደም መመረዝ ምክንያት ከፍተኛ የግፊት መቀነስና እራስን በሚስቱ ግዜ
  • ፕሮቴስት የሚባለው እጢ( በወንዶች) በማበጡ ምክንያት የሽንት ፍሰት ሲዘጋ
  • አንዳንድ ለኩላሊት መርዛማ የሆኑ መድሃኒቶችን ሲወስዱ ወይም ለኬሚካል ሲጋለጡ እንዲሁም ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የደም ግፊት የሚያስከትሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ነው፡፡

 ከራሚ የኩላሊት ጉዳት

ኩላሊትዎ ከ3 ወር ለረዘመ ግዜ  ተግባሩን በትክክል መወጣት በማይችልበት ግዜ ከራሚ የኩላሊት ጉዳት ( መዳከም) አጋጥሞታል ይባላል፡፡ ምንም እንኳን ለህክምና ወይም ለማከም የሚቀለው በግዜ ሲደረስበት ቢሆንም ምልክቶቹ ግን በአብዛኛው በግዜ አይታዩም ከራሚ የኩላሊት ጉዳትን ከሚያስከትሉት ውስጥ የስኳር በሽታና የደም ግፊት ተጠቃሾቹ ናቸው፡፡

  • የስኳር በሽታ በቁጥጥር ስር ካልዋለ ከፍተኛው የስኳር መጠንና አላስፈላጊ የሆኑ ቆሻሻዎች በኩላሊት ላይ ጫና በመፍጠር ጉዳት ያደርሳሉ፡፡
  • የደም ግፊት በበኩሉ በትንንሾቹ የኩላሊት የደም ስሮች ላይ የሚያሳድረው ውጥረትና መሸርሸር ኩላሊቱን ስራወን በአግባቡ እንዳይሰራ ያደርገዋልወይም ይጎዳዋል ከነዚህ በተጨማሪ ሌሎች እንደ ምክንያ ከሚቀመጡት ውስጥ
  • ከሰውነት መከላከያ ህዋሳት በኩላሊት ላይ ጉዳት እንዲደርስ የሚያደርጉ የተለያዩ በሽታዎች
  • ለረጅም ግዜ የቆዩ የቫይረስ ኢንፌክሽኖች(አንደ ኤች አይ ቪ/ ኤድስ)
  • የተለያዩ የኩላሊት ውስጥ ትቦ ኢንፌክሽኖችና በኩላሊቱ አካላዊ ይዘት ላይ የሚከሰቱ የተፈጥሮ መዛባቶችና የመሳሰሉት ከራሚ የኩላሊት ጉዳት ወይም መድከምን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡

ምልክቶቹ

የድንገተኛ የኩላሊት ጉዳት ምልክቶች

  • የሽንት ፍሰት መዘጋት ወይም በጣም መቀነስ
  • የአይንና የእግር እብጠት
  • ትኩሳትና ጠቅላላ የአካል ህመም ስሜቶች ይጠቀሳሉ፡፡

ከራሚ የኩላሊት ጉዳት ምልክቶች

ይህ ጉዳት መጀመሪያ አከባቢ ምልክቶች ሊያሳይ ባለመቻሉ አስቸጋሪ የሚያደርገው ሲሆን ጉዳቱ እየቆየ ሲሄድ የሚታዩት ምልክቶች የሚከተሉትን ይመስላሉ፡፡

  • የማቅለሽለሽና ተደጋጋሚ ትውከት
  • ሽንት የመሽናት ድግግሞሽ በከፍተኛ መጨመር እና አረፋማ ሽንት
  • የአይን እና የእግር እብጠት
  • ከፍተኛ የድካም ስሜት
  • ምክንያት የሌለው ከፍተኛ የክብደት መቀነስ
  • የተለየ የቆዳ መድረቅ እና መሳሳት
  • የምግብ ፍላጎት መቀነስ
  • የምግብ ጣዕም ማጣት የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡

እነኚህን ምልክቶች ባዩ ግዜ ( ምንም እንኳን በሌላ ምክንያትም ሊከሰቱ ቢችሉም) ሃኪምዎትን በፍጥነት ማማከር ተገቢ ነው፡፡ በተለይ የስኳር እና የደም ግፊት በሽታዎች ካለብዎ እንዲሁም የኩላሊት በሽታ በቤተሰብ ያለ ከሆነ ፈጣን የህክምና እርዳታ ያስፈልግዎታል፡፡