የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ፎረም በዛሬው ዕለት ተጠናቋል

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከኦሮሚያ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በጅማ ከተማ ያዘጋጀው የ2013 በጀት ዓመት 1ኛው የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ፎረም ከጥቅምት 12-14/2013 ተካሂዶ በተሳካ ሁኔታ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡

ፎረሙን በንግግር የከፈቱት የኦሮሚያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ ዶ/ር ጉሻ ቤላኮ በንግግራቸውም ወደ ታሪካዊዋ የአባ ጅፋር ከተማ እንኳን በሰላም መጣችሁ በማለት በአሁኑ ወቅት ኮቪድ-19ን ከመከላከል በተጨማሪ በፎረሙ ሌሎች የሕብረተሰብ ጤና ስጋቶችን እንደ ቢጫ ወባ፣ ወባ፣ ሚዝል፣ ወዘተ ያሉትን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር እና መከላከል እንጻር የተሰሩ ስራዎች በፎረሙ ወቅት እንደሚታዩ ተናግረዋል፡፡
በመቀጠልም የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ በበኩላቸው ባለፉት 8 ወራት እንደ ሀገር ብሎም እንደ ዓለም ከፍተኛ የጤና ስጋት በመሆን የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈና በመቀጠፍሰደ ላይ ስላለው የኮቪድ-19 በሽታን ሀገራችን በተቀናጀ መልኩ እንዴት መቆጣጠር እንደቻለች ጠቅሰዋል፡፡ በተጨማሪም እንዴት በመተባበር መስራት እንዳለብን እና ያለፈውን አመስግነን ለቀጣዩ መዘጋጀት እንዳለብን በጽሁፍ የተደገፈ ማብራሪያ አድርገዋል፡፡
በፎረሙ የተሳተፉ ክልሎች በየክልላቸው የሕብረተሰብ ጤና አደጋን ከመቆጣጠር አንጻር የተሰሩ ስራዎችን እንዲሁም ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ያቀረቡ ሲሆን በነዚህም ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸው የመፍትሄ ሀሳቦች ተቀምጠዋል፡፡
በስተመጨረሻም ኢንስቲትዩቱ የታብሌት ኮምፒውተሮችን ለክልሎች ሰራ ማሳለጫ እንዲሆኑ ከሰጠ በኋላ ተሳታፊዎች የጅማ ዩኒቨርስቲን የሄልዝ ኬር ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ማዕከልንና የጅማ ቤተ መዘክርን ጎብኝተዋል፡፡