"የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ልጆች" - ታሪክን ወደኋላ

"የሐኪም ወርቅነህ እሸቴ ልጆች" - ታሪክን ወደኋላ

በፎቶው ላይ የሚታዩት በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ዶክተር ማርቲን ወርቅነህ እሸቴ ልጆች ናቸው። ዶክተር ማርቲን ወርቅነህ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ዶክተር ሲሆኑ ወላጆቻቸው ከጎንደር የአፄ ቴዎድሮስ ወታደር ሆነው በመቅደላ ጦርነት ላይ የተሰው ናቸው።
.
ያኔ ዶክተር ወርቅነህ የሁለት አመት ልጅ ነበሩ ፣ አፄ ቴዎድሮስ ሞተው የእንግሊዝ ወታደሮች መቅደላ አምባን ሲቆጣጠሩ ህፃኑ በሚቃጠሉ ቤቶችና በሞቱ ሬሳዎች መሃል እያለቀሱ አገኟቸው።
.
ማርቲን እና ቻርለስ የተባሉ ጓደኛሞች አፈፍ አድርገው ከሚቃጠሉት ቤቶች መሃከል አንሷቸው ፣ በኃላም ወደ እንግሊዝ አገር ይዘዋቸው ሄዱ። በሁለቱ ባነሷቸው ስዎች ስም ማርቲን ቻርለስ ተብለው እየተጠሩ አደጉ ፣ ተምረውም በህከምና ዶከተር ሆነው ተመረቁ።
.
ከብዙ አመት በኃላ ወደ አገራቸው ተመለሱ ደጉ ንጉሥ አፄ ምኒልክም በክብር ተቀበሏቸው። ወዲያውኑ ወላጆቻቸውን ፍለጋ ተያያዙት ፣ ሲያጠያይቁ ወላጆቻቸው በመቅደላው ጦርነት እንደሞቱ አያታቸው ግን ጎንደር እንደሚኖሩ ይሰማሉ። ጎንደር ተጉዘው አያታቸውን ያገኛሉ። ስማቸውም ወርቅነህ እንደነበረ የአባታቸው ስምም እሸቴ ይባል እንደነበር አያታቸው አስረዷቸው።
.
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ሃኪም ወርቅነህ እሸቴ እየተባሉ ይጠሩ ጀመር። አዲስአበባ ተመልሰው ብዙ አመት ኖሩ አገራቸውንም በህክምና አገለገሉ። በኃላ በእንግሊዝ የኢትዮጵያ አምባሰደር ሆነው ተሹመው ለንደን ሄዱ።
.
ከታች ያለው ፎቶ ጊዜው ጣልያን ኢትዮጵያን የወረረበት ጊዜ ነው። የሃኪም ወርቅነህ ልጅ የሆነው ዮሴፍ ወርቅነህ ለወንድሞቹና እህቶቹ ጥሊያን ኢትዮጵያን እንደወረረች ከእንግሊዝ ጋዜጦች ያገኘውን እያነበበላቸው እነሱም ተመስጠው እየሰሙት ነው።
.
ነገር ግን ጋዜጣ አንብቦ ዜናውን እንደሰማ አርፎ መቀመጥ አልሆነለትም። የአብራሪነት አጭር ኮርስ እዛው እንግሊዝ አገር ተምሮ ለመዋጋት አገሩ ገባ። የኢትዮጵያ መንግስትም ከነበሩት ጥቂት የውጊያ አውሮፕላኖች አንዷን እንዲያበር እድል ሰጠው። ማይጨውን ጨምሮ ብዙ በረራዎችን አደረገ። በመጨረሻም የሚያበረው አውሮፕላን በጠላት ተመቶ ሲወድቅ ለሚወዳት አገሩ ተሰዋ።