"የከብት ወተት ለከብት ልጅ ብቻ: የእናት ጡት የማጥባትን ጥቅም በቅጡ እናውቃለን?"

የጡት ማጥባት ጥቅም ከሳይንስ ግንዛቤና ትንተና በላይ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሮ ታላቅ በሆነው የወሊድ ክስተት ወቅት የቀመረችው ትልቅ ስጦታ ነውና፡፡

በሳይንሳዊ ፍተሻ የተደረሰባቸው 10 የጡት ማጥባት በረከቶች ደግሞ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡፡
.
1. ህጻናትን ጡት ማጥባት ህጻናቱ ከበሽታ የተጠበቁ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ የእናት ጡት ወተት ለህይወት አስፈላጊ የሆኑትን ሁሉንም ቫይታሚኖችንና ንጥረነገሮችን ብቻ ሳይሆን ህጻናቱ ከበሽታ የተጠበቁ እንዲሆኑ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮችንም ይዟል፡፡ የጥናት ውጤቶች እንደሚያሳዩት የእናት ጡት ወተት የጠቡ ህጻናት በሆድ ውስጥ ቫይረስ፣ በጆሮ ኢንፌክሽኖች፣ በታችኛው የመተንፈሻ አካላት ህመምና በማጅራት ገትር ህመም የመጠቃት ዕድላቸው አነስተኛ ሲሆን በበሽታዎቹ ቢጠቁም እንኳ ህመሙ አይጸናባቸውም፡፡ ህጻናትን ጡት የማጥባት በረከት ከህጻንነት እድሜም አልፎ በኋለኛው ዘመን የሚከሰቱ እንደ ታይፕ 1 እና 2 የስኳር በሽታንና ከፍተኛ የኮልስትሮል መጠንንም እንዳይከሰት ይዋጋል፡፡
.
2. ጡት ማጥባት ህጻናት በአለርጂ እንዳይጠቁ ይከላከላል፡፡
.
3. ጡት ማጥባት የህጻናትን የአእምሮ ብቃት ከፍ ያደርጋል፡፡ ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የእናታቸውን ጡት በደንብ የጠቡ ህጻናት በአእምሮ ብቃት መፈተኛ እና በቋንቋ መመዘኛዎች ላይ ከፍተኛ ውጤት ሲያስመዘግቡ ተስተውሏል፡፡ ከዚሁ ጋር የተያያዘው እጅግ አስደናቂው ነገር ለረጅም ጊዜያት ጡት የጠቡ ህጻናት አነስ ላለ ጊዜ ከጠቡት ይልቅ የአእምሮ ብቃታቸው የላቀ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
.
4. የእናት ጡት ወተት የጠቡ ህጻናት ካልጠቡት ይልቅ በህጻንነት ከሚያጋጥም አለቅጥ የመወፈር አደጋ የተጠበቁ ናቸው፡፡ የእናት ጡት ወተት የጠቡ ህጻናት በሰውነታቸው ውስጥ በርካታ ሌፕቲን በመኖሩ ሳቢያ የሰውነታቸው ስብ ክምችትና የምግብ ፍላጎታቸው የተመጠነ ይሆናል፡፡
.
5. ህጻናትን የእናት ጡት ወተት መመገብ Sudden Infant Death Syndrome በተሰኘው ድንገተኛ የህጻናት ሞት ሰበብ የመሞት እድልን ይቀንሳል፡፡
.
6. ህጻናትን ጡት ማጥባት እናቲቱንም ከድብርትና የመጨናነቅ መንፈስ ይገላግላል፡፡ ልጅን እየተንከባከቡ በማጥባት ወቅት ሰውነት ውስጥ የሚመነጨው ኦክሲቶሲን የተሰኘው ሆርሞን የደም ግፊትን ይቀንሳል፡፡
.
7. ጡት የሚያጠቡ እናቶች ከጡት፣ ከማህጸን ካንሰርና ከበርካታ የካንሰር ዓይነቶች የተጠበቁ ናቸው፡፡
.
8. ጡት ማጥባት የአጥንት መሳሳትን ይከላከላል፡፡ እናቶች በሚያጠቡበት ወቅት የአጥንት ማዕድናት እጥረት ቢያጋጥማቸውም፣ የጡት ወተት መመንጨት ከቆመ በኋላ የአጥንት ውስጥ የማዕድን መጠን ከበፊቱ የበለጠ ስለሚሆን በኋለኛው ዘመን ላይ የሚያጋጥም የአጥንት መሳሳትን ይከላከላል፡፡
.
9. ጡት ማጥባት የሰውነት ክብደት እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ በእርግዝና ወቅት የሚከሰተው የሰውነት ክብደት መጨመር ጡት በማጥባት ወቅት ይቀንሳል፡፡
.
10. ጡት ማጥባት ወጪ ቆጣቢ ነው፡፡
.
መልካሙን ሁሉ ተመኘው