ኮቪድ በሽታን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የሴክተር መስሪያ ቤቶች የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው ተባለ

ሕብረተሰቡ ለኮቪድ-19 በሽታ የሚሰጥው ትኩረት እና የቅድመ መከላከል ጥንቃቄዎች ከዕለት ወደ ዕለት እየቀነሰ በመምጣቱ የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረትና ርብርቦሽ አዳጋች እያደረገው መምጣቱ ተገለፀ፡፡

ዶ/ር ሊያ ታደሰ የጤና ሚኒስትር በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ ከልዩ ልዩ ሴክተር መ/ቤቶች ጋር በተደረገው የጋራ የምክክር መድረክ ላይ እንዳስገነዘብት ህብረተሰቡና ተቋማት ለኮቪድ-19 በሽታ የሚሰጡት የቅደመ መከላከል ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ የተነሳ የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረትና ርብርብሽ አዳጋች እያደረገው እንደመጣ አስታውቀዋል፡፡
በመሆኑም ማንኛውንም አገልግሎት ለማግኘት ከተፈለገ በሁሉም ተቋማትና ግለሰቦች ደረጃ ማስክ ማድረግ ግዴታ የሚሆንበት አካሄድ በቅርቡ እንደሚተገበር አብራርተዋል፡፡ ይህም አካሄድ ህብረተሰቡን ከበሽታው ለመጠበቅ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ እንደታመነበት ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡
ወ/ሮ ሳህረለ አብዱላሂ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር የኮቪድ 19 በሽታን መከላከል አስመልክቶ በየተቋማቱም ሆነ በማህበረሰቡ ዘንዳ መዘናጋቶች እንደሚስተዋሉ አስረድተው በቀጣዩ ስድስት ወራት መከናወን ባለባቸው ተግባራት ውስጥ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ፡ የአፍና የአፍንጫ የመከላከያ ጭንብልን በማድረግ እንዲሁም እጅን በአግባቡ በመታጠብ እና መሰል ወሳኝ የሆኑ ተግባራትን አጠናክሮ በመቀጠሉ በኩል የሴክተር መ/ቤቶች ሚና ወሳኝነት እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡
አቶ አስቻለው አባይነህ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ም/ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው መድረኩ የተዘጋጀበት ዋና አላማ የኮቪድ-19 የመከላከል ስራዎች በበርካታ መ/ቤቶች  በባለቤትነት እና በእቅድ የሚመራበትን አካሄድ ለማመቻቸት እንደሆነ አስረድተው በሽታውን በመከላከል ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ይቻል ዘንድ የሴክተር መስሪያ ቤቶች በመከላከል ስራው ላይ ያላቸውን ተሳትፎ መጎልበት ወሳኝነት እንዳለው ተናግረዋል ፡፡
በመሆኑም በቀጣይነት ሁሉም ሴክተር መ/ቤቶች ከዚህ በፊት ይተገብራቸው የነበረውን እንቅስቃሴዎች ይበልጥ በመቀጠል የበሽታውን የመከላከል ሥራ የሚያከናውነውን የየመ/ቤቶቻቸውን ግብረ ሀይል በማጠናከር፡ ከሌላቸውም በማቋቋም እንዲሁም በተቀናጀ መልኩ በጋራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ ለእዚህም በሁሉም ተቋማት ዘንዳ የሚሰሩ የቅድመ መከላከል ስራዎች በሙሉ በተቀናጀና በህብረት ለመስራት የሚያስችላቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
በእዚሁ የጋራ መድረክ ላይ የኮቪድ በሽታን ለመከላከል እስከአሁን ድረስ የተሰሩ ስራዎች ዋጋ የሚኖራቸው ቀጣይነትና ተከታታይነት ባለው መልኩ ሁሉም ተቋማትና የማህበረሰብ ክፍሎች ጉዳዩ ያገባኛል እና ይመለከተኛል በሚል መንፈስ በመንቀሳቀስ የመከላከል ስራውን ሲተገብሩ እንደሆነ አጽንኦት ተሰጥቶበታል፡፡