ለሚጥል በሽታ ተገቢው ትኩረት መሰጠት አለበት ተባለ፡፡

የሚጥል  በሽታ ህሙማን በሀገራችን ተገቢው ሰብዓዊና ህገመንግስታዊ መብታቸው ተጠብቆ ለልማቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና የልማቱም ተጠቃሚ

እንዲሆኑ እንዲሁም በማህበረሰባችን ውስጥ በሚጥል ህመም ላይ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት በማስወገድ በየትኛውም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ዘርፍ የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
ዶ/ር ኤባ አባተ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጠîና ኢንስትትዩት ዋና ዳይሬክተር በሚጥል ህመም  ዙሪያ በሀገራችን ለስድስተኛ ጊዜ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ ለአንድ ሳምንት  “በሚጥል ህመም ለተጎዱ ድምፅ ነኝ!” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችና ፕሮግራሞች የሚከበረውን ብሄራዊ የሚጥል ህመም ሳምንት ፕሮግራም በክብር እንግድነት በመገኘት በከፈቱበት ወቅት እንደተናገሩት የሚጥል ህመም ህክምና የታማሚውን ቤተሰብና የህብረተሰቡን ድጋፍ ጭምር የሚጠይቅ በመሆኑ ህመሙ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ ይቻል ዘንዳ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ስለህመሙ ያለው የተሳሳተ አመለካከትና ግንዛቤ መለወጥ፣ ህሙማንን በወቅቱ ወደ ጤና ድርጅቶች ሄደው ምርመራና ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የሚጠበቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህ ሲሆን በህመሙ ምክንያት የሚከሰተው የአካል ጉዳትና ህመም መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሀና ደምሴ  የኢትዮጵያ ነርቭ ሀኪሞች ማህበር ፕሬዝዳንት በበኩላቸው የህክምና ግልጋሎት በወቅቱ ከተሰጠ ከሰባ በመቶ በላይ  ህሙሙን በሽታውን ተቆጣጥረው ጠናማ ህይወት መምራት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡
አቶ እዮብ  አስራት የኬር ኤፕለፕሲ  ኢትዮጵያ ም/ኃላፊ ኬርኤፕለፕሲ ኢትዮጵያ የሚጥል ህመም በአገራችን እያደረሰ ያለውን ማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ስፋትና ጥልቀት በመመልከት በህመሙ የሚሰቃዩ ኢትዮጵያውያን የጤና ሁኔታ እንዲሻሻል፤ የሚጥል ህመምን ማከም የሚችሉ የባለሙያዎች ቁጥር በጤና ተቋማት ላይ እንዲጨምር ስልጠና በመስጠት፣ የህክምና እድሎችን በማመቻቸትና፣ ስለህመሙ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለው አስተሳሰብና አመለካከት እንዲቀየር ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም ህመሙ እንዳይከሰት የመከላከል ሥራ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ2019 በወጣው የአለም ጤና መረጃ ዘገባ መሰረት በዓለም  አቀፍ ደረጃ 50 ሚሊዮን ያህል የሚጥል ህመም ያለባቸውን ሰዎች ያጠቃል፡፡ ከእነዚህ መካከል 80 ፐርሰንት ያህሉ በታዳጊ ሀገራት ይገኛሉ ፡፡ በተጨማሪም 90  የሚሆኑት ታካሚዎች በአፍሪካ የሚገኙ ሲሆን ህክምናውን አያገኙም፡፡ በኢትዮጵያ በሚጥል ህመም ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን ህመሙ እንዳለባቸው ይገመታል፡፡