የትልቁ አንጀት ካንሰር /Colorectal cancer

የአንጀት ካንሰር በአለማችን በሶስተኛ ደረጃ በስፋት ሰዎችን የማያጠቃ የካንሰር ዓይነት ሲሆን በወንዶች ከሳንባና ከፕሮስቴት ካንሰር ቀጥሎ ሲገኝ በሴቶች ደሞ ከሳንባና ከጡት ካንሰር ቀጥሎ የካንሰር ደረጃውን ይይዛል ።

በተጨማሪም በአለማችን ሁለተኛው በከፍተኛ ደረጃ ገዳይ ካንሰር በመሆኑም ይታወቃል ።በምዕራቡ አለም በእድሜ የገፋ ሰዎችን ቢያጠቃም በሀጠራችን በተደረጉ ጥናቶች ግን ከ50% በላይ የሆኑት የዚህ በሽታ ታማሚዎች እድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች ሆኖ ተገኝቷል ።

አጋላጭ ነገሮች

1.እድሜ፦ አብዛኞቹ የዚህ ህመም ተጠቂዎች እድሜያቸው ከፍ ያለ ቢሆንም በወጣቶችም አልፎአልፎ ይከሰታል
2.በቤተሰብ ፦እስከ 20% የሚሆኑት የዚህ በሽታ ታማሚዎች የቤተሰብ ታሪክ ያላቸው ሲሆን 80% የሆኑት ግን ምንም ዓይነት የቤተሰብ ታሪክ የላቸውም ።
3.የሰኳር በሽታ ፦በተለይ ውፍረትን ተከትሎ የሚመጣ የስኳር በሽታ ያለባቸው ሰዎች ስኳር ከሌላቸው ሰዎች አንፃር ከፍ ያለ የአንጀት ካንሰር ተጋላጭነት አላቸው ።
4. የአልኮል መጠጥ ማዘውተር
5.ማጨስ
6.ለረጅም ጊዜ ቀይ ስጋ አዘውትሮ መመገብ
7.ለረጅም ጊዜ የሚቆይ የአንጀት ቁስለት/ Crohns disease and ulcerative colitis

ምልክቶች

1. በመጀመሪያ ደረጃ ያለ ካንሰር ምንም ምልክት ሳያሳይ በኮሎኖስኮፒ(የትልቁ አንጀት ምርመራ ዓይነት ) ብቻ ሊታወቅ ይችላል ። ለዚህም ነው እድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ምንም ምልክት ባይኖራቸውም የኮሎኖስኮፒ ምርመራ እንዲያደርጉ የሚመከረው ።
2.የሆድ ህመም ፦የቁርጠት ዓይነት ለረጅም ጊዜ የቆየ ህመም ትኩረት ይሻል ።
3.የሰገራ ሁኔታ መቀያየር ፦ አንዳንዴ እንደ ተቅማጥ አንዳንዴ ደሞ የሆድ ድርቀት ለረጅም ጊዜ መኖር
4.ከሰገራ ጋር ደም መቀላቀል
5.ሰገራ ሲቀመጡ መስማጥ
6. ድካም ፦ይህም ለረጅም ጊዜ በማድማት የተነሳ የደም ማነስ በማስከተሉ ነው።
7. የሆድ ማበጥ ፦ በተለይ በቀኝ የታችኛው የሆድ ክፍል ያበጠ ነገር መኖር
8.የአንጀት መዘጋትና ፈስም ሆነ ሰገራ መከልከል
9. የአንጀት መበሳት አስከትሎ ሊወሳሰብም ይችላል ።

ማስታወሻ ፦ ከላይ የዘረዘርኳቸው ምልክቶች ሁሎም በአንድነት ላይገኙ ይችላል። በተጨማሪም የተጠቀሱት ምልክቶች ለተጨማሪ ምርመራ መነሻ ነገሮች እነጂ ማረጋገጫ አይደሉም ።

ምርመራ

1. ብዙ ዓይነት የደም ምርመራዎች
2.ኮሎኖስኮፒ
3.ፓቶሎጂ፦ የናሙና ጥናት
3.አልትራሳውንድ
4. CT scan
5.ራጅ
6.MRI

የበሽታው ደረጃዎች

በሽታው አራት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን ደረጃው ከፍ ባለ ቁጥር የመዳን ዕድሉ እየቀነሰ ይሄዳል።

የህክምና አማራጮች
1.ቀዶ ህክምና ፦ይህም በሽታውን ለመከላከል ፣ለማዳን ወይም ለማስታገስ /Palliative surgery ።20 በመቶ የሚሆኑት ድንገተኛ ኦፕራሲዮን ያስፈልጋቸዋል ። ወቅታዊ /ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የሰገራ መውጫ በሆድ በኩል ሊሰራም ይችላል ።
2. መድኃኒት / Chemotherapy ፦ይህም በአብዛኛው ከኦፕራሲዮን በኋላ የሚሰጥ ሲሆን ከኦፕሬሽን ያመለጡ የካንሰር ሴሎችን ይገድላል ።
3. የጨረር ህክምና ፦ ይህ በተለይ የታችኛው ትልቁ አንጀት ካንሰር ሲከሰት ይሰጣል ።