ተጨማሪ ምግብ እና የመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት በህፃናት

ተጨማሪ ምግብ ስንል ምን ማለት ነው? የተመጣጠነ ምግብ ማለት ምን ማለት ነው? የልጅዎን አጣ ፋንታ ስለሚወስነው የመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ምን ያህል በቅጡ ያውቃሉን?

የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት ከእርግዝና የመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ ሁለተኛ ዓመት የልደት ቀን ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል። በነዚህ ቀናት የሚደረጉ እንክብካቤዎችና የአመጋገብ ሁኔታዎች የህይወታችን ቀሪ ዘመን ላይ ወሳኝ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ወርቃማዎቹ የመጀመሪያ አንድ ሺ  ቀናት በመባል ይጠራሉ፡፡

እነዚህ ቀናት ለምን ወሳኝ እና እጅግ ጠቃሚ ሆኑ?

ከፍተኛ የሆነ አካላዊ ፣ አእምሮአዊ እና የማህበራዊ ክህሎት እድገት የሚመዘገብበት። የቀጣይ ህይወታችን መሠረት የሚጣልባቸው ቀናት ናቸው።

ሀገራችን ብቁ ምርታማና ጥራት ያለው ትውልድ እንድታፈራ በነዚህ 1000 ቀናት ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይጠበቅብናል።
   
ተጨማሪ ምግብ ማለት ልጆች 6 ወር ከሞላቸው በኋላ ከእናት ጡት ወተት በተጨማሪ ተጨማሪ ምግብ መስጠት ማለት ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የእናት ጡት ወተት ብቻ ከ6 ወር በኋላ ለልጆች በቂ ስላልሆነ፡፡  

አንድ ህፃን 6 ወር ከሞላው በኋላ ተጨማሪ ምግብ መጀመር ተገቢ ነው ምክንያቱም ከእናት ወተት ወይም ከፎርሙላ በተለይም አይረን (iron) እና ተጨማሪ ጉልበት የሚሠጡ ነገሮችን ከወተት ብቻ ማግኘት ስለማይችሉ ነው፡፡ ነገር ግን የእናት ጡት ወተት ቢያንስ እስከ 2 አመት ድረስ ሊወስዱ ይገባል፡፡

በዚህ የእድሜ ክልል ህፃናት እድገታቸው ፈጣን ስለሚሆን በቂ የሆነ ምግብ ካላገኙ ለስውነታቸው የሚሆን በቂ  ኃይል (calorie) አያገኝም። በተጨማሪም  ሰውነታቸው ለመቀጨጭ እና መቀንጨር ይዳረጋል።

በተጨማሪም የበሽታ የመከላከያ ሀይላቸው (Immunity) ዝቅተኛ ስለሚሆን ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ተጋላጭ ይሆናሉ።

ሕጻናት ከ6 ወር በፊት ሌሎች ምግቦችን ቢጀምሩ ችግር ይኖረዋል?

አዎን!  ከ6 ወር በፊት ሌሎች ምግቦችን መጀመር  ለተቅማጥ እና ትውከት: የጡት ወተት መቀነስ እና የመሳሰሉት ችግሮችን ያስከትላል።

ሕጻናት ተጨማሪ ምግቦችን ዘግይቶ ቢጀምሩ ጉዳቱ ምንድነው?

ህፃኑ በቂ የሆነ ክብደት እንዳይጨምር እና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች (minerals) እና ቫይታሚን እጥረት እንዲያጋጥመው ያደርጋል። ይሄም የራሱ ከሆነ ከፍተኛ የጤና ችግርን ያመጣል።

በየትኛውም የእድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ ህፃናትም ሆነ አዋቂዎች የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል::

የተመጣጠነ ምግብ ማለት መሰረታዊ የሆኑ የምግብ ክፍሎችን የሚያካትት ነው:: ካርቦአይድሬት (ሃይል ሰጪ ምግቦች ) ፣ ፕሮቲን (ሰውነት ገንቢ) ፣ የዘይት እና ቅባት ምግቦች ፣ ቫይታሚን እና ማህድን (በሽታ ተከላካይ) እና በቂ ወሃ ናቸው። ከነዚህ ንጥረ ነገሮች በቀን ወስጥ ከ4 አይነት ሊያገኝ ይገባል።

ልጆችን እንዴት ተጨማሪ ምግብ እናስጀምራቸው?

ከላይ የተጠቀሱትን የምግብ አይነቶች በተለያየ መንገድ ማዘጋጀት ይቻላል። በሀገራችን የተለመደው አሰራር የምጥን ዱቄት ይባላል:: ይሄም በውስጡ የተለያዩ ከእህል ዘሮችን ማካተት ይቻላል ለምሳሌ 3 እጁን ከእህል ዘሮች ማለትም የተፈተገ ስንዴ ÷በቆሎ ÷ማሽላ ÷ጤፍ ÷አጃ እና የመሳሰሉት አድርጎ አንድ እጁን ደሞ ከጥራጥሬ አይነቶች ለምሳሌ ባቄላ ÷ሽንብራ÷ አተር÷ ምስርን ÷ኦቾሎኒ አድርገን ማዘጋጀት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችን መጨመር እንችላለን፡፡

ልጅዎ ተጨማሪ ምግብ ስናጀምር በቀን ውስጥ ምን ያህል መጠን  መውሰድ አለባቸው?

ከ 6 - 8 ወር ያሉ :- ከ 2 - 3 የቡና ሲኒ  ☕️
ከ 9 ወር - 1 ዓመት :- ከ 4-5 የቡና ሲኒ☕️
ከ 1 ዓመት በላይ ግን በሲኒ መለካት አስፈላጊ አይደለም ሆኖም ግን 3 ዋና ዋና የምግብ ሰዓቶችን ጠብቆ በመስጠት በተጨማሪ ደሞ በመሃል በመሃል 2 መክስሶችን መስጠት ይገባል::

እድሜያቸዉ 6 - 8 ወር ላሉ ህፃናት ከአጥሚት ትንሽ ወፈር ያሉ ምግቦች ይመከራሉ ::

እድሜያቸው 8-12 ወር ለሆናቸዉ ደሞ በከፊል ጠጣር (semi solid) ወይም ለስለስ ያለ ገንፎ በቀን 4-5 ጊዜ መመግብ ይቻላል ፡፡

በተቻለ መጠን የታሸጉ ምግቦችን (Processed food) ትተን በተፈጥሮ ከእህል ዘሮች ከተዘጋጁ እና በተለመዶው ምጥን ከሚባሉ ምግቦች ብንጀምር መልካም ነው:: እነዚህ ምግቦች በቀላሉ የሚፈጩ እና በዉስጣቸው ከፍ ያለ የብረት ማእድን ስለሚይዙ የደም ማነስን ይከላከላሉ። በተጨማሪም ኃይል ሰጪ (carbohydrate) እና ገንቢ (protein) የሆኑ ምግቦች ናቸው::

ልጆች የእህል ዘሮችን ከለመዱ በዋላ በስለዉ የተፈጩ አትክልቶችን ቀስ በቀስ ማስለመድ ተገቢ ነው::

ይህን ምግብ ለማዘጋጀት የእናት ጡት ወተትን ወይም ፎርሙላን በመጠቀም ማዘጋጀት እንችላለን።

ሌላው ደግሞ በቂ ውሃ መስጠትን መዘንጋት የለብንም።

ቤተሰብ ልብ ማለት ያለበት ሁል ጊዜ መጀመሪያ በተቻለ መጠን የእናት ጡት ከጠቡ በኃላ መሆን አለበት ተጨማሪ ምግብን መስጠት ያለብን።

ተጨማሪ ምግብ ስናስጀምር ልናደርጋቸው እና ልናውቃቸው የሚገቡ ነገሮች ምንድናቸው?

1. ልጆች በመጀመሪያ ምግብ ለመጀመር የሚያስችሉ ምልክቶች እንዳላቸው ማረጋገጥ። ለምሳሌ ጭንቅላታቸወን ሙሉ ለሙሉ መደገፍ አለባቸው። ምግብ ሲያዩ የመዞር ምልክት ያሳያሉ በዚህ ጊዜ ምግብ ማስጀመር ተገቢ ነው፡፡

2. ተጨማሪ ምግብ በምንሰጣቸው ጊዜ ልጆች ደስተኛ እና የተረጋጉ በሚሆኑበት ሰዐት መሆን አለበት፡፡

3. ምግብ ስናስጀምር በአንድ ጊዜ አንድ አይነት ምግብ ብቻ  ከ3 -5  ቀናት መስጠት አለብን። ምክንያቱም አንድ አይነት ምግብ ከሰጠናቸው ለምግቡ አላርጂ ከሆኑ እንዲሀም የሚስማማቸውን እና የማይስማማቸውን ምግብ ለመለየት ስለሚረዳ።

4. በመጀመሪያ ትንሽ ትንሽ ወይም 1-2 የሾርባ ማንኪያ ብቻ እየሰጠን ምግቡን ማላመድ አለብን ይህንንም ስንሰጥ ሁል ጊዜ ጡት ካጠባናቸው በኋላ መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ተጨማሪ ምግቡን መስጠት አለብን ከዛም ቀስ እያልን በቀን ከ2-3 ጊዜ መስጠት እንችላለን።
ቤተሰብ ልብ ሊል የሚገባው የመጀመሪያ ሁለት ወራት ልጆችን የተለያዩ የምግብ አይነቶችን በማዘጋጀት የተለያዩ ጣዕሞችን እንዲያጣጥሙ ለማድረግ እንጂ ብዙ እንዲበሉ መጠበቅ የለበትም።

5. ልጆች በመጀመሪያ ምግብ እምቢ ሊሉ ይችላሉ አንድን ምግብ ልጆች አልወደዱትም ለማለት ቢያንስ ያንን ምግብ ከ 10-12 ጊዜ መሞከር አለብን፡፡ እንዲሁም ትልቅ ትግስት ያስፈልጋል ።

6. ልጆች ምግብ እንዲመገቡ ማስገደድ የለብንም ነገር ግን በተቻለ መጠን እንዲመገቡ ማበረታታት አለብን፡፡

7. ጣፋጭ ምግቦች ማብዛት የለብንም። ጣፋጭ ምግብ የሚያበዙ ልጆች ማግኘት ያለባቸውን ንጥረነገር አይወስዱም ምክንያቱም ጣፋጭ ምግቦች የምግብ ፍላጎት የመዝጋት ባህሪ ስላላቸው።