የቢጫ ወባ በሽታ

የሎው ፊቨር ወይም ቢጫ ወባ የሚባለው በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣና የመድማት ችግር የሚያስከትል በወባ ትንኝ አማካኝነት የሚተላለፍ የትኩሳት በሽታ ነው።

ትንኟ በበሽታው ከተያዘ ሰው ደም በምትመጥበት ጊዜ በተህዋሲያኑ ትያዛለች፤ የተህዋሲያኑ ተሸካሚ የሆነች የወባ ትንኝ ከጤነኛ ሰው ደም ለመምጠጥ ቆዳውን በምትበሳበት ጊዜ የሚተላለፍ በሽታ ነው።
• በሞቃታማ ስፍራ በሚገኙ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች፣
• በስራ ወይም መኖሪያ ቦታ ረግረጋማና የአቆረ ውሃ፤
• በየቦታው የተጣሉ ውሃ የሚያቁሩ ቁሳቁሶች፣
• በማይከደኑ የውሃ ማጠራቀሚያ እቃዎች ለትንኞች መራቢያነት ምቹ ስፍራዎች ናቸው።
የቢጫ ወባ በሽታ ምልክቶች፡
የመጀመሪያ ከ3 እስከ 4 ቀናት የሚከሰቱ፡-
• በድንገት የሚከሰት ትኩሳት
• ብርድ ብርድ የሚል ስሜት፣
• ራስ ምታትና አጠቃላይ የሰ ውነት ህመም፣
• የጀርባና የጡንቻ ህመም፣
• ማቅለሽለሽና ትውከት ዋናዎቹ ናቸው።
በሁለተኛ ደረጃ የሚከሰቱት፡-
• የትኩሳት ማገርሸት፤
• የሰውነት ወይም ዓይን ቢጫ መሆን (juandice)፤
• የሰውነት (ከዓይን፣ አፍ፣ አፍንጫ፣ ወ.ዘ.ተ.) መድማትና
• ደም የተቀላቀለበት ትውከት ናቸው።
• የበሽታው ምልክት የታየባቸው ሰዎች በአስቸኳይ የሕክምና እርዳታ በጤና ተቋማት ካላገኙ ራስን መሳትና ብሎም ሞት ያስከትላል።
የቢጫ ወባ በሽታ መከላከያ መንገዶች፡-
በሽታው እጅግ አስተማማኝ የሆነ፤ ምንም ጉዳት የማያስከትል፣ በአንድ ጊዜ የሚወሰድና ለበሽታው የዕድሜ ልክ የሰውነት መከላከያ የሚፈጥር ክትባት በመከተብ፤ በሽታውን መከላከል ይቻላል።
ትንኟ እንዳትራባ መቆጣጠር፡-
• ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ቁሳቁሶችን ማስወገድ፣
• ውሃ ያቆሩ ስፍራዎችን ማጠንፈፍ /ማድረቅ/፣
• ለወባ መራቢያ ምቹ የሆኑ ስፍራዎችን ፀረ-ተባይ ማስርጨት፣
• በቤት ውስጥ የወባ መግደያ ፊሊት መርጨት።
የትንኟን ንክሻ መከላከል፡-
• እጀሙሉና ረጅም ልብሶችን መልበስ
• ትንኝ ማባራሪያ የሰውንት ቅባት መጠቀም፤
• በማንኛውም ስዓት የአልጋ አጎበር በመጠቀም መተኛት፤
• መኖሪያ ቤትን የትንኝ መግደያ ፍሊት በመርጨት ትንኞችን ማስወገድ፤
የበሽታው ምልክቶች እንደታዩ በአስቸኳይ በአቅራቢያ ወደሚገኝ ጤና ተቋም በመሄድ ሪፖርት ማድረግና ሕክምና ማግኘት ከበሽታው ለመዳን ስኬታማ ለውጥና ፈውስ ለማግኘት ወሳኝ ተግባር ነው።